መዝሙር
የመንፈሳዊ ምስጋና ትምህርት
መዝሙር ምንድን ነው?
መዝሙር ማለት ምስጋና ማለት ነው። ልዩ ልዩ ስልትና ቃና ባለው ድምጽ የሚዜም በዜማ ዕቃ የሚቀርብ መንፈሳዊ ማኅሌት ነው። በመዝሙረ ዳዊት እንደተመዘገበው «ለእግዚአብሔር በምስጋና ዘምሩ» የሚል ትዕዛዝ ይገኛል። (መዝ 146፥7) ከዚህ ሌላ ቅዱስ ያዕቆብ «ደስ የሚለው ማንም ቢኖር እርሱ ይዘምር» በማለት ጽፏል። (ያዕ 5፥13) ስለዚህ ለክርስቲያን መዝሙር የዘወትር ተግባሩ ሊሆን ይገባል። መዝሙር በክርስቲያን አምልኮ ውስጥ ከፍተኛ ቦታ አለው። እስራኤላውያን ከጥንት ጀምሮ በተለይም ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከፀሎትና መጽሐፍን ከማንበብ ጋር መዝሙርን በመዘመር እግዚአብሔርን ያመልኩ ነበር። በክርስትናም ከስብከቱ፣ ከፀሎቱ፣ ከስግደቱ ... ጋር አብዛኛው የአምልኮታችን ክፍል መዝሙር ነው። መዝሙር ምስጋና እንደመሆኑ መጠን በግልና በሕብረት ከፀሎት ጋር ለእግዚአብሔር የሚቀርብ መስዋዕት ነው። (ቈላ 4፥2) በብሉይ ኪዳን እንደሚታወቀው የፍሪዳ ወይም የጊደር፤ የበግና የፍየል መስዋዕት በተለያየ ምክንያት ለእግዚአብሔር ይሰዋ ነበር። ነገር ግን ከዚህ ይልቅ እግዚአብሔር ትሑትና የዋህ በሆነ በተሰበረ ልብ የሚቀርብ የከንፈራችንን ፍሬ እርሱም የምስጋና መስዋዕትን እንድናቀርብለት በቃሉ ነግሮናል። (መዝ 49፥14። ዕብ 13፥15 ። ሆሴዕ 14፥2) ብዙዎች ግን መዝሙርን ጊዜ ማሳለፊያ፣ የፕሮግራም መሸጋገሪያ፣ መዝናኛ አድርገው ይዘምሩታል። ይህም ዘማሪው በመዝሙር ሳይሆን በሌላ ሥራና ሃሳብ መጠለፉንና መዝሙርን ግን በተጨማሪነት የሚሰማው የሚዘመረው መሆኑን ያሳያል። እግዚአብሔር ግን ከመዘመራችን በፊት የእኛ ሰውነት ሕያው ቅዱስም መስዋዕት ሆኖ እንዲቀርብለት ይፈልጋል። (ሮሜ 8፥12) መጽሐፍ ቅዱስ እግዚአብሔር ወደ አቤልና ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ ይለናል እንጂ ቀጥታ ወደ መስዋዕቱ ተመለከተ አይለንም (ዘፍ 4፥4) የእኛ ሕይወት ግን ከዝማሬው ላይ ሳይሆን ብንዘምር እንዲሁ የከንፈር ድካም ብቻ ስለሆነ እንደ ቃየል መስዋዕት ተቀባይነት አይኖረውም። እግዚአብሔር ሌሎችን እንስሳት ለአንክሮ ለተዘክሮ ሲፈጥር ሰውና መላእክትን ግን የፈጠረው ክብሩን እንዲወርሱና ስሙን እንዲቀድሱ ነው። ቅዱሳን መላእክት ሱራፌልና ኪሩቤል ሁልጊዜ አዲስ ቅኔና «ቅዱስ ቅዱስ ቅዱስ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር» በማለት ድምጻቸውን ከፍ አድርገው በመጮኽ እየዘመሩ እግዚአብሔርን እንደሚያመሰግኑት ተዘግቧል። (ኢሳ 6፥1-5 ። ራዕይ 4:8-11 # መዝ 102፥20) ሰማያውያን መላእክት እንዳመሰገኑት ሁሉ ምድራዊያን ሰዎችም ለእግዚአብሔር አዲስ ምስጋናን ማቅረብ ይገባናል። «ምድር ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት» ይላል (መዝ 95፥1-2) በእርግጥ ሌሎችም ፍጡራን በሰማይና በምድር ያሉት ሁሉ እግዚአብሔርን አመስግኑት ተብለዋል። (መዝ 148፥1-13) ሆኖም ከሰውና ከመላእክት በስተቀር የእግዚአብሔርን ክብር የመውረስ ዕድል ስለሌላቸው ምስጋናቸው ጊዜያዊ ነው። ሰውና መላእክት ግን የተፈጠሩት እግዚአብሔርን በማመስገን እንዲኖሩ ነው። ስለዚህ እኛም እንደ ቅዱስ ዳዊት «በየቀኑ ሁሉ እባርክሃለሁ፤ ስምህንም ለዘላለም ዓለምም አመሰግናለሁ» በማለት ልናመሰግን ምስጋናም የዘወትር ሥራችን ሊሆን ይገባል።
መዝሙር እንዴት መዘመር አለበት?
ሐዋርያው ቅዱስ ጳውሎስ «በምትሰበሰቡበት ጊዜ ለእያንዳንዱ መዝሙር አለው ይላል። (1ኛ ቆሮ 14፤26) ደግሞም በመዝሙርና በመንፈሳዊ ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ ይላል። (ቆላ 3፤16 ። ኤፌ 5፤19) እንዲህ ከሆነ ክርስቲያኖች ለአምልኮትም ሆነ ለወንጌል ስብከት በቤተ ክርስቲያን ሲሰበሰቡ እንዲሁም በማኅበር እና በግል መዘመር አለባቸው። ነገር ግን ክርስቲያኖች ሲሰበሰቡ ለእያንዳንዱም መዘመር ለእያንዳንዱም ትምህርት አለውና መዝሙር የጸጋ ስጦታቸው የሆነ ተሰባስበው መዘምራን በመሆን ሊያገለግሉ ይችላሉ። ቅዱስ ዳዊት በመገናኛው ድንኳን እንዲያገለግሉ ያደራጃቸው መዘምራን ነበሩ (2ኛ ዜና 29፤25-28) ወንዶችም ሴቶችም መዘምራን መሆን ይችላሉ። የጾታ ልዩነት የለም። ከባቢሎን ምርኮ በኋላ ከተመለሱት እስራኤላውያን ሁለት መቶ ወንዶችና ሴቶች መዘምራን ነበሩ። (ዕዝራ 2፤65-66) በዚህ መሠረት ቤተ ክርስቲያን የካህናት መዘምራን አሏት። እንዲሁም በየሰንበት ትምህርት ቤቱ ቋሚ የወንዶችና የሴቶች መዘምራን አሏት።
ስለ መዘምራን አገልግሎት
በአጭሩ ስለመዘምራንና ስለመዝሙር ይህን ያህል ካየን አሁን ደግሞ «መዝሙር የሚዘምሩት ሰዎች እንዴትና ምን መሆን አለባቸው» የሚለውን የመዘምራንን ነገር እንመልከት። መዘምራን ከመዘመራቸው በፊት የመዝሙርን ምንነት ማወቅ ዜማን ብቻ ሳይሆን ቃሉን ማስተዋል ለምን ለማን እንደሚዘምሩ ማወቅ ዘምረው ምን እንደሚያገኙ መረዳት አለባቸው። የመዝሙርን ምንነት ያላወቀ ዘማሪ መዝሙር ጊዜ ማሳለፊያ ወይም መዝናኛ ሆኖ (መስሎ) ሊታየው ይችላል። እንዲህ ዓይነት ሰው በመዘምራን መካከል ካለ መዘምራን ተገንዝበው የሚዘምሩት መዝሙር ሌሎች እንዳይድኑበት እንቅፋት ሊሆን ይችላል። ይሆንማል። መዝሙርን መጀመሪያ ያስተማረው እግዚአብሔር ነው ሰው አይደለም። ማናኛውም ዘማሪ በሚዘምርበት ጊዜ ያንን መዝሙር እግዚአብሔር በአፉ ውስጥ እንዳስቀመጠለት መገንዘብ አለበት። ዘማሪው እንደዘፈን የሚቆጥረውና ያልተረዳው ከሆነ የሚዘምረው መዝሙር ሰዎችን በፍቅረ እግዚአብሔር የሚያጠምድ አይሆንም። የሚዘምረውን መዝሙር የማያውቅ ከሆነ እየዘመረ እንኳ ዓይኑ ይቅበዘበዛል። ሰውን ብቻ ይመለከታል። ዘሩ (ቃሉ) እና ዜማው ይደናገረዋል። ስለዚህ አገልግሎት ሰዎችን በማቅረብ ፈንታ ሰዎችን የሚገፋ ይሆናል። ዘማሪው ከዚህ ሁሌ እንዲድንና እንዲጠበቅ መዝሙሩን በሚገባ ማወቅ አለበት። ይህም ማለት ዜማንና ዘሩን ብቻ ሳይሆን በማን ፊት እንደሚዘምር ማወቅ አለበት። መዘምራን የምእመናንን ልብ ለእግዚአብሔር ቃል የለሰለሰ መሬት ለማድረግ በዝማሬ ማረሻ የሚያርስ እና የሚቀሰቀስ የሚያለሰልስ መሆን አለባቸው። በሚያሳዝነው መዝሙር ላይ የደስታፊት ገጽታ፤ በሚያስደስተው _ መዝሙር ላይ የሐዘን የትካዜ ገጽታ ሊታይባቸው አያሰፈልግም። የሰውነታቸው ሁኔታ (እንቅስቃሴ) በመዝሙሩ ጋር የሚሄድ መሆን አለበት። በተለይ ግን መዘምራን የመድረክ ላይ ክርስቲያን ብቻ እንዳይሆኑ መጠንቀቅ አለባቸው። በአሁኑ ሰዓት ትልቅ የቤተ ክርስቲያን ችግር የሰባኪያን እንደስብከታቸው፤ የመዘምራን እንደመዝሙራቸው አለመሆን ነው። «ጹሙ ወጸልዩ ለእግዚአብሔር ተቀነዩ» ጹሙና ጸልዩ ለእግዚአብሔርም ተገዙ ብሎ ጠዋት የዘመረው ለሰዓት በኋላ ደግሞ ሲጾም ሲጸልይ ለእግዚአብሔር ሲገዛ አይታይም። ይህ የሚሆንበት ምክንያት ዘማሪው የሚዘምረው ዜማውን ብቻ እንጂ ቃሉን ጭምር ስላልሆነ ነው። እግዚአብሔር ከዜማ በፊት የሚያየው የሚያዜመውን ሰው ሕይወት ነው። በዝማሬ የሚታለል (የሚሸነገል) አምላክ አይደለም። የመዘምራኑ የውስጥ ሕይወት ከመዘመራቸው በፊት በመንፈስ ቅዱስ ኃይል የለዘበ፣ የጣፈጠ እና ልዑል እግዚአብሔር ሕዝብን የሚባርክበትና የሚለውጥበት ልቦና ሊኖራቸው ይገባል። መዘምራን የድምፅ የአለባበስ፣ የአቋቋም የአፍ አከፋፈት ተወዳዳሪዎች መሆን የለባቸውም። ሱራፌልና ኪሩቤል የሚያመሰግኑትን ጌታ ለማመስገን ከእርሱም ጋር ለመነጋገር የተቀደሰ አንደበትና የተተኮሰ ከንፈር ነው የሚያስፈልገው። (ኢሳ 6፤5-7) መዝሙር የሚዘምረው ለእግዚአብሔር በእርሱ ፊትና በእርሱ ቤት የሚዘመር ምስጋና ነው። በቤቱ የሚዘመር የተቀደሰ ሕይወት ነው። መዘምራን በሚዘምሩበት ጊዜ ከፊታቸው ሰማያዊ ንጉስ ኢየሱስ ክርስቶስ አለና በሥጋ ሳይሆን በመንፈስ እንዲቆሙ ጊዜ ወስደው መጸለይ አለባቸው። ያለዚያ ግን በዚያ በእግዚአብሔር መድረክ ላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ጋርደው እነርሱ ለመታየት የተዘረጉ መጋረጃዎች ይሆናሉ ማለት ነው። የእግዚአብሔር አገልጋይ ደግሞ ዓላማው የእግዚአብሔር ነጸብራቅ መሆን ስለሆነ እንደመስታወስ የእግዚአብሔርን ብርሃን የሚያንፀባርቅ ሕይወት ሊኖራቸው ይገባል። አቤት መዘመራቸው (አቤት አሰላለፋቸው) ለመባል ብቻ መድረክ ላይ የሚወጡ መጎናጸፊያቸው ክርስቶስ ኢየሱስ ያልሆነ መዘምራን ለማኅበራቸውም ሳይቀር የውድቀት ምክንያት ይሆናል። ስለዚህ በአገልግሎታቸው ሁሉ የእግዚአብሔር መንፈስ ጎልቶ እንዲታይ በመዝሙራቸው ያዘኑ እንዲጽናኑ፤ የተሰበሩ እንዲጠገኑ፤ የተጠራጠሩ እንዲያምኑ ዘወትር በፍቅርና በሰላም በመንፈስ በኅብረት በመጸለይ የተጉ፣ የማይተማሙ፣ የማይኮራረፉ መሆን አለባቸው። እንዲህ ከሆነ የሚዘምሩት መዝሙር የእስር ቤት መሰረት የሚያናውጥ ሰንሰለት የሚበጥስ ነፍሳትን የሚያድን ይሆናል። (የሐዋ ሥራ 16፤16-34) በዚህ ዓለም ያሉ ሰዎች በመሪዎችና በነገሥታት ፊት ዘፍነውና ቦርቀው የሚሰጡአቸው ጊዜያዊና ኃላፊ የሆነ የኃጢአት ውጤት ነው። (ማቴ 14፤1-12) ለእግዚአብሔር መዘመር ግን በምድር ሰላም እና የሕሊናን ዕረፍት በመጨረሻም የዘለዓለምን ሕይወት ያቀዳጃል ያወርሳል። («አገልግሎት» በዲያቆን እንግዳ ቸሩ ገጽ 4-5)። መዘምራን ልክ እንደ ወንጌል ሰባኪዎች እንደሌሎችም አገልጋዮች በክርስቲያኑ ሕዝብ ሕይወት ውስጥ ከፍተኛ አገልግሎት ይሰጣልና በመንፈሳዊ ሕይወታቸው የታነጸና ለሌላው ብርሃን መሆን የሚችሉ እንዲሆኑ በጾምና በጸሎት ሊተጉ ይገባል።
ማጠቃለያ
«ዘምሩ ለአምላክችን ዘምሩ፤ ዘምሩ ለንጉሣችን ዘምሩ» (መዝ 47፥6)። እግዚአብሔር ዘለዓለማዊ አምላክና ንጉሥ ነው። ስለዚህ ምስጋናውም ከዘለዓለም እስከ ዘለዓለም ነው። እግዚአብሔር በባሕርይው የተመሰገነ ነው። ስለዚህ ብናመሰግነው የምንጠቀመው እኛ መሆናችንን ልናስተውል ይገባናል። እስከ አሁን ድረስ ስለመዝሙር ያለውን መጽሐፍ ቅዱሳዊና ትውፊታዊ ትምህርት አይተናል። ነገር ግን ይህ ትምህርት ስለመዝሙር በጥልቅ እንድናውቅ ሳይሆን በማስተዋል እንድንዘምር ለማድረግ የተሰጠ ትምህርት ነው። መዝሙር በሰውና በእግዚአብሔር መካከል ያለ ሃይማኖታዊ ፍቅር የሚገለጽበት መንገድ ነው። በእኛ ላይ ያለው ዓለማዊ ፍቅር ነው። (መኃልየ 2፤4) በላይ ቤትና በታች ቤት ዜማ በሌሎችም የዜማ ልዩነቶች እየተጣላንና እየተነቃቀፍን ጥዑም የሆነውን ማኅሌት ፍቅር አልባ ልናደርገው አይገባም። በየሰንበቱ ትምህርት ቤቱም በሚፈጠሩ የዜማ ልዩነቶች ምክንያት ፍቅርን በማደፍረስ እግዚአብሔርን እናመስግን ብንል የከንፈር ምስጋና ይሆናል። መዝሙሮች ሁሉ አንድ ወጥና ተመሳሳይ ያሬዳዊ ዜማ እንዲኖራቸው የሚመለከታቸው ሁሉ ጥረት ሊያደርግ ይገባል። ከዚህም ሌላ እውነትንና እውነተኞችን እየተጸየፉና እየጠሉ ድኃ እየበደሉ ጻድቃን እያጨነቁ ፍርድ እያጣመሙ እግዚአብሔር ሁሉን እንደሚወድ ፍቅሩን በማስተዋል የሚዘመረው መዝሙር በእግዚአብሔር ተቀባይነት የለውም። (አሞጽ 5፤23) ስለዚህ በዚህ ሁሉ ለሰማያዊው ንጉሥ ለእግዚአብሔር በፍቅር መዘመራችንን ልናስተውል ይገባል። አንዳንድ ጊዜ መዝሙር ሲዘመር ከመጠን በላይ ጩኸት ሲበዛ በሰሜት በመነዳት ከሥርዓት ውጪ መሆን ይታያል። ይህ ማንን እንደምናመሰግን፣ እንዴት እንደምናመሰግን ምን እያልን እንደምናመሰግን ካለማስተዋል የተነሳ ነው። ስለዚህ የምንዘምረውን ምን እያልን እንደምናመሰግን አምላክ እግዚአብሔርን በኪሩቤል ጀርባ ላይ እንዲሁም በመስቀል ዙፍን ላይ ሆኖ በዓይነ ልቦና እያየነው፤ በግላችንም ሆነ ከዓለም ጋር ያደረገልንን ውለታ እያስታወስን በማስተዋል ልንዘምር ያስፈልጋል። የስብከታችን ማዕከል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንደሆነ ሁሉ የመዝሙራችንም ማዕከል እርስ ሊሆን ይገባዋል። ወደ ቅዱስ ያሬድ ከተላኩት ወፎች አንዷ «አዲሱን የእግዚአብሔር ምስጋና ሥራ እርሱም የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ስም ነው» ብላ እንደነገረችው መረዳት ይኖርብናል። (ያሬድና ዜማው ገጽ 23) በመጽሐፍ ቅዱስም «በመዝሙርና በዝማሬ በመንፈሳዊ ቅኔም ቅኔ በጸጋው በልባችሁ ለእግዚአብሔር ዘምሩ እግዚአብሔር አብን በእርሱ እያመሰገናችሁ በቃል ቢሆን ወይም በሥራ የምታደርጉትን ሁሉ በጌታ በኢየሱስ ስም አድርጉት» የሚል ቃል ይገኛል። (ቆላ 3፤17) ስለዚህ ስሙን በትሕትና እየጠራን በመስቀል ፍቅሩ እንዳዳነን እያሰብን በከንፈር ብቻ ሳይሆን በልብ በማስተዋል እንዘምርለት። አንድ መዝሙር ታሪክ ምስጢርና መልዕክት ይኖረዋል። ይህም በመዝሙር ቃል ውስጥ ከላይ እስከታች ተያይዞ የሚገኝ ነው። ስለዚህ ዜማውን ወይም አዘማመሩን ብቻ ሳይሆን ታሪኩ ምስጢሩና መልዕክት ምን እንደሆነ እያስዋልን መዘመር አለብን። ቅዱስ ዳዊት «እዘምራለሁ ንጹሕ መንገድንም እስተውላለሁ» ብሏል። (መዝ 100፤2)
ወስብሐት ለእግዚአብሔር ... አሜን።